
የሀዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በድግሪና ዲፕሎማ ፕሮግራም በተለያዩ የጤና ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 642 ተማሪዎችን ለ30ኛ ዙር በምረቃ መርሐግብሩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ተማሪዎቹን ያስመረቁት የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ እንዳሉት ጤናማ ፣አምራችና የበለፀገ ማህበረሰብ የማፍራት ራዕያችንን የሚናሳካው በሰለጠነ የሰው ሀይል በመሆኑ ይህንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ለማህበረሰባችሁ ጤና ዘብ የምትቆሙ፣ህዝባችሁን በመልካም ስነምግባር፣ በርህራሄና በቅንነት የምታገግሉ መሆናችሁን አውቃችሁ መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል በማለት ለተመራቂዎቹ መልዕክት አስተላልፏል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የማህበረሰቡን የጤና ጥያቄ ለመመለስ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ በተለይም "ለላቀ ውጤትና ለጥራት እንስራ" በሚል መርህ ሰፊ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ሀላፊዋ ኮሌጁ ዘንድሮ ለ30ኛ ዙር ያስመረቃቸው ባለሙያዎች ለኢኒሼቲቮቹ ስኬት በተመደቡበት የሙያ አይነት በትጋትና በአገልጋይነት መንፈስ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሀዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ወ/ሮ ትሁን ፈለቀ በበኩላቸው በ1972 ዓ.ም በጤና ረዳትነት ተማሪዎችን በማስተማር የጀመረው ኮሌጁ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደረጃውንና እና የስልጠና አድማሱን በማስፋት በአሁኑ ጊዜ በስድስት የድግሪ እና ሰባት የዲፕሎማ ፕሮግራሞች በርካታ በስነምግባር የታነፁ ብቁ ባለሙያዎችን በጥራት በማሰልጠን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ የሚገኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በኮሌጁ በመጀመርያ ዲግሪና ዲፕሎማ በተለያዩ የትምህርት አይነቶች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ ተመራቂዎች ውስጥ 57.5% በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ፣ የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚዎችም ሴቶች መሆናቸው የምረቃ ፕሮግራሙን ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
ዲኗ አክለዉም ተመራቂዎቹ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የድካማቸውን ፍሬ የሚያዩበት ዕለት መሆኑን በመጥቀሰ የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ገልፀው፣ የተማሩት ሙያ በሰው ህይወት ላይ የሚወስኑበት ስለሆነ አገልግሎታቸውን የሚሻውን ማህበረሰብ ያለምንም አድሎዎ በከፍተኛ ሙያዊ ሥነ-ምግባርና ርህራሄ እንደሚያገለግሉ እምነታቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ማራዶና ዘለቀን ጨምሮ የክልሉ ጤና ቢሮ ማኔጅመንት አባላት፣ የአቻ ኮሌጅ ሀላፊዎች፣ የኮሌጁ የስራ ሀላፊዎች፣ መምህራን፣ ሰራተኞችና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከናውናል።
ነሀሴ 3/2017 ዓ.ም
ሀ.ጤ.ሳ.ኮ